ፍልስፍና
ከWikipedia
ፍልስፍና የሚለው ቃል ከግሪኩ "Philos" ማለትም ፍቅር እና፣ "sophos" (ጥበብ) የተገኘ ውሁድ ነው። በቀጥታው የጥበብ ፍቅር ወይም ፍቅረ ጥበብ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በመሆኑም ፍልስፍና እውቀትን፣ እውነትን፣ ጥበብን መውደድ፣ መሻት፣ መመርመር ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ይህ የጥናት ክፍል በዋናነት ነገሮችን በመላምታዊ መንገድ ለመመርመር ይሞክራል። የፍልስፍናን ምንነት ለማወቅ የሚጠይቃቸውን ዋነኛ ጥያቄዎች እንመልከት።
ይዞታ |
[ለማስተካከል] ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች
ፍልስፍና የሚመረምራችው አምስት ዋነኛ ቁምነገሮች ህላዌ፣ ግብረገብ፣ እውቀት፣ እውነት፣ እና ውበት ናቸው። ፈላስፋዎችን ለብዙ ዘመናት ሲያስጨንቁ ከቆዩ ጥያቄዎች ውስጥ
- እውነት ምንድር ነው? አንድን አስተያየት ለምንና እንዴት እውነት ወይም ሃሰት መሆኑን እናውቃለን? ጥበብስ ምንድር ናት?
- አዋቂነት የሚቻል ነገር ነውን? ማወቃችንን እንዴት እናውቃለን? አዋቂነት የሚቻል ነገር ከሆነ የታወቀ እና ያልታወቀ ማለት ምንድር ነው? ከታወቀው ያልታወቀውን እንዴት መሻት እንችላለን?
- ግብረገብ በሆነው እና ባልሆነው መካከል ልዩነት አለን? ካለስ ልዩነቱ ምንድር ነው? የትኞቹ ድርጊቶቻችን ናቸው ልክ? ልክ ያልሆኑትስ የትኞቹ ናቸው? ሥነምግባራዊ መስፈርቶች ቋሚ ናቸው ወይስ ተነፃፃሪ? እንዴትስ መኖን አለብኝ?
- ገሃድ የሆነው ምንድር ነው? የገሃድ ነገሮች ተፈጥሮአቸው እንዴት ያለ ነው? እውን አንዳንድ ነገሮች ከኛ ግንዛቤ ውጭ መኖር ይቻላቸዋልን?
- ውበት ምንድር ነው? ውብ የሆኑ ነገሮች ከሌሎቹ በምን ይለያሉ? ሥነጥበብ ምንድር ነች? ሃቀኛ ውበት የገኛልን? የሚሉት ናቸው።
እነዚህ ከላይ በደፈናው የተጠቀሱ ጥያቄዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው አመክንዮአዊ፣ ሥነ-እውቀታዊ፣ ሥነ-ምግባራዊ፣ ሥነ-ኃልዮአዊ፣ እና ሥነ-ውበትአዊ በመባል ይታወቃሉ። ምንም እንኳን እነዚህ ዋነኞቹ ጥያቄዎች ይሁኑ እንጂ ብቸኞቹ አይደሉም። በተጨማሪም በመካከላቸው አንዳንድ መደራረብ ይታያል። ታዋቂው የግሪክ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ ሥነ-መንግሥት፣ ሥነ-ተፈጥሮ፣ ሥነ-ምድር፣ ሥነ፡ሕይወት፣ ሥነ-አየር እና ሥነ ፈለክ የፍልስፍና ክፍሎች ናቸው ብሎ ያምን ነበር።
ሌሎች የፍልስፍና ባህሎች ከምዕራባውያን ፍልስፍና በተለየ በነዚህ ጉዳዮች ላይ በዙም አላተኮሩም። ምንም እንኳን የሂንዱ ፍልስፍና በዚህ አንፃር ከምዕራባውያኑ ቢመሳሰለም እስከ 19ኛው ምዕት-አመት ድረስ በኮሪይኛ፣ በጃፓንኛ፣ እና በቻይንኛ ውስጥ "ፍልስፍና" የሚል ቃል ይገኝ አልነበረም። በተለይ የቻይና ፈላስፎች ከግሪኮቹ ለየት ያለ የምደባ ስርዓት ይከተሉ ነበር።
[ለማስተካከል] ፍልስፍናዊ ባህሎች
[ለማስተካከል] የምዕራቡ ዓለም ፍልስፍና
የምዕራቡ አለም ፍልስፍና የሚጀምረው ከግሪኮች ሲሆን የመጀመሪያው ፈላስፋ ተብሎ የሚታወቀው ታሊዝ ነው። ይህ ሰው የኖረበትን ጊዜ ለማወቅ ብዙም አስቸጋሪ አይደለም። ይኸውም በ585 ከክ.ል በፊት የፀሃይ ግርዶሽ እንደሚኖር በመተንበዩ ከዚህ ጊዜ የተወሰነ አመት ቀደመ ብሎ ማይሌጠስ በተባለችው የትንሹ እስያ (የአሁኑ ቱርክ) ክፍል እንደተወለደ የታወቀ ነው። ታሊዝ ዓለም እና በውስጡ ያሉ ነገሮች ሁሉ ከውሃ እንደተፈጠሩ ያምን ነበረ። ከሱ በኋላ የተነሱ የግሪክ ፈላስፎች የሱኑ መንገድ በመከተል ዓለም ከአንድ ወይም ከሌላ ነገረ እንደተፈጠረች አስተምረዋል። ለምሳሌ አናክሲሜነስ የዓለም ጥንተመሰረቷ አየር ነው ሲል፣ ሄራቅሊጠስ እሳት ነው ብሏል። አናክሲማንደር ከነዚህ ሁሉ ለየት በማለት የዓለም መሰረቷ ይህ ነው የማይባል "apeiron" ወይም የትየለሌ የሆነ ነገር ነው ይላል።
የምእራቡን ዓለም ፍልስፍና እስክ 1900 ድረስ ቅርጽ እንዳስያዙ የሚነግርላቸው ፈላስፋዎች የሚከተሉት ናቸው፡
ሶቅራጥስ፣ አሪስጣጣሪስ፣ ፕላጦ፣ አክዊናስ፣ ኤራስመስ፣ ማኪአቬሌ፣ ቶማስ ሞር፣ ሞንታጝ፣ ግሮቲየስ፣ ዴካርት፣ ሆበስ፣ ስፒኖዛ፣ ሎክ፣ ሌብኒሽት፣ በርክሌ፣ ሑሜ፣ ቮልቴይ፣ ሩሶ፣ ካንት፣ ሺለር፣ ሄግል፣ ሾፐናዎር፣ ጆን ኦስቲን፣ ጄ.ኤስ. ሚል፣ ኮምቴ፣ ዳርዊን፣ ማርክስ፣ እንግልስ፣ ፍሬደሪሕ ኚሼ፣ ዱርካሂም.